Friday, January 11, 2019

የስልጤ ህዝብ ታሪክ

የስልጤ ህዝብ ታሪክ

ክፍል  ሁለት

#የስልጤ ገራዳዊ ሥርዓት

ኢማም አህመድ በተሸነፈበት ዘመን ብዙ የሕዝቦች (በተለይም የኦሮሞ)

እንቅስቃሴ ተከስቶ ነበር። የኢማሙ የጦር አበጋዞች ከነሠራዊታቸውና

የእስልምና ሚሺነሪዎች (ዳኢዎች) በኡምናን፥ በወለኔ፥... አካባቢዎች

ሰፍረው ነበር። እነዚህ ቡድኖች ከሐረር ጋር የነበራቸው ግንኙነት በአርሲዎች

(አርሲዎች ስልጤን ‘ሀደሬ’ ብለው እንደሚጠሩት ልብ ይሏል) በመቋረጡ

ወይም በሌላ ምክንያት ወደ ሐረር ሳይመለሱ ቀሩ። ይህ ሌላ ታሪካዊ ሁኔታን

ፈጠረ።

ወደ ሐረር ያልተመለሱት የኢማም አህመድ ግራኝ የጦር አበጋዞች ኀይላቸውን

አጠናክረው ገራዳዊ ሥርዓት (አካባቢያዊ መንግሥት) መሠረቱ። እነዚህ

መሪዎች ግን ሱልጣኖች ሳይሆን ገራዶች ይባሉ ነበር።

የመጀመሪያው የገራዳዊ ሥርዓት ማዕከል ኡምናን (ኡምናን አዘርነት ውስጥ

የምትገኝና የሀጂ አሊዬ መካነ መቃብር የሚገኝባት ታሪካዊ ሥፍራ ናት)

ሲሆን መሪውም ሀዲ ገራድ (ሀጂ) አሊዬ ኡመር ነበሩ። ስልጤ የሚለው

ስምም በዚያ ገራዳዊ ሥርዓት ውስጥ ተፀንሶ ያደገ በመሆኑ ገራዳዊው

ሥርዓት ለስልጤዎች ልዩ ትርጉም አለው። ምክንያቱም ‘ሱልጣኔት’

የሚለውን የሀዲያ ግዛት አሻራ የያዘ በመሆኑና ራሳቸውን ከሌላው ‘ሀዲያ’

የሚለዩበት በመሆኑ ነው። ስልጤ የሚለው ቃል ሱልጣኔት ከሚለው ቃል

የመጣ ነው። ስልጤ የሕዝቡ ብቻ ሳይሆን የአገሩም መጠሪያ መሆኑ መዘንጋት

የለበትም።

ይህ ገራዳዊ ሥርዓት እስከ 1881 ቀጠለ። እዚህ ጋ አንድ ነገር ለናስታውስ

ፈለግን፤ ይሀውም ስልጤ የነባር ሕዝቦችና የመጤዎች ድብልቅ መሆኑን ነው።

ነባሩ ሕዝብ ሀገር (ባንዳንድ ቦታ ዠራ) ተብሎ ሲጠራ መጤዎቹ አጃሞ

በመባል ይታወቃሉ።

#የሸዋ መንግሥት መፈጠር

የሸዋ መንግሥት መፈጠር በተለይ የአጼ ምኒልክ ወደ ደቡብ መስፋፋት

በእነአምደ ጽዮንና በሐዲያ ሱልጣኖች መሃል የተከሰተውን ዓይነት ችግር

በምኒልክና በስልጤ ገራዶች መሃል ፈጠረ። በዚህም የተነሣ የሙስሊሞችና

የምኒልክ ጦር ተደጋጋሚ ጦርነቶችን አደረጉ (ከሐሰን እንጃሞ ጎን ስልጤዎች

ተሰልፈው ተዋግተዋል)።

በመጨረሻም ጋሮሬ ወንዝ አካባቢ በተደረገ ጦርነት የስልጤ ገራዶች ለምኒልክ

ለመገበር ተገደዱ። ይህን ጦርነት ስልጤዎች ‘ያንሰንበት አማረ’ (የቅዳሜው

ወረራ) ብለው ይጠሩታል። በጦርነቱም ጤም ለዝቦ ጨነቆ በመባል

የሚታወቁት የስልጤ ገራድ ተሰዉ። በመሪያቸው መሞት የተነሣ ስልጤዎች

መሸነፋቸውን አምነው ለምኒልክ ገበሩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስልጤ የሸዋ

ግዛት አንዱ አካል ሆነ። ገራዳዊውም የስልጤ ሥርዓት ተደምስሶ ባለባታዊው

የአጼዎች አገዛዝ በቦታው ተተካ።በወቅቱም እንዲህ ተብሎ ተገጥሞ ነበር፤

ጎበነ ያማድ፥

ደሌ ተላማርድ፥

ገበብኝ ባሮት።

ዪሊሎይ ሸአብዶ፥

በፋፍ ቀልብ ኤለ እንዶ፥

ዶንደ አግሬን እንዶ፥

ጎቤን በጉማይዶ።

አንሰበተይ ቅለ፥

እመጫን ሚሽ አለ፥

ባራሀ ክተ ብለ፥

ዩርባታሀ ባለሀ አለ።

አማረ የወንበር፥

ገባን የቦለት በር።

ፋፈው ኤጋሀ ክንብል፥

አራስ ጩሎሽ ተንቀል፥

አራሽ ኡርፈከ የንቀል።

ትርጉሙም፤

(ራስ) ጎበና ለጥጋቡ፥

ወገቤን ሳልታጠቅ (ሳልዘጋጅ)፥

በማታ መጣብኝ (ወረረኝ)።

ሼህ አብዶ ኢሊሌ (የሰው ስም)፥

ጀግና አእምሮ የለውምን?

ጥላ ጋሻ ሆኖ ነው ጎበናን በጉማጅ የገጠሙት።

(ሼህ አብዶ በዚያን ጊዜ በጀግንነት ከተዋጉት አንዱ ነበሩ)

ቅዳሜ ጎህ ሲቀድ፥

የሚመጣ ሰው አለ፥

ምሳህን በደንብ ብላ፥

ስለእራትህ የሚያውቀው ፈጣሪ ነው።

አማራ ለሥልጣን
‘ቦለት በር’ (የቦታ ስም) ገብቷል።

ጀግና እባክህን መክት፥

አራስ ልጇን ታንሳ፥

ገበሬም እርፉን ያንሳ።

ስልጤ በምኒልክ ጦር ከተሸነፈ በኋላ ብዙ በደል ተፈጽሞበታል፤ ሀብቱ

ተዘርፏል፥ ገራዱ ተገድሏል፥ መሬቱም ተነጥቆ ለጭሰኝነት ተዳርጓል።

ነገር ግን የትግሬው አጼ ዮሐንስ በወሎ ሙስሊሞች ከፈጸሙት የጭካኔ

ድርጊት ጋር ሲነፃፀር የምኒልኩ ሻል ያለ ነበር። በዘመኑ ብዙ የወሎ

ሙስሊሞች ወደ ስልጤ (ይህም ለእስሊምና መጠናከር በተጨማሪነት

አገልግሏል) አገር በስደት መጥተው ነበር።

አምደ ጽዮን እንዳደረጉት ሁሉ ምኒልክም ሕዝቡን በዐይነ ቁራኛ የሚጠብቁ

ነፍጠኞችን በስልጤ ምድር ላይ አሰፈሩ። ስልጤዎችን የጐዳው ሌላው ነገር

ደግሞ የምኒልክ ጦር ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ የሚያደርገው ዘመቻ ሁሉ

በስልጤ በኩል አልፎ ይደረግ ስለነበር ጦሩ ሲዘምትም ሆነ ከዘመቻ ሲመለስ

ይፈጽም የነበረው ዘረፋ ሕዝቡን ለከፋ ችግር ዳረገው።

........ይቀጥላል..........

#ምንጭ---------መህማቾት ከሚለው መፅሃፍ የተወሰደ

     ዋቢ- መጽሐፍት

1. Survey of Ethiopia and The Horn II, Addis Ababa University.

2. ፈድሉ ኑር፥ የስልጤና አዘርነት–በርበሬ ተረትና ምሳሌ፥ 1964

(ለመመረቂያ ያዘጋጁት)።

3. ዶክተር ላጵሶ ግ. ድሌቦ፥ የኢትዮጵያ ረጅም የሕዝብና የመንግሥት

ታሪክ፥ አዲስ አበባ፥ 1982።

4. Mengesha Rikitu, Oromo Oral Treasvre, June 1992, London,

England.

5. ዶክተር አብርሃም ሁሴንና ሀብታሙ ወንድሙ፥ ያዘርነት በርበሬ ባህልና

ታሪክ፥ ቦሌ ማተሚያ ድርጅት።

6. William A. Shack; The Gurage, Oxford University Press, 1966.

7. ሁሴንና አወል፥ 'ጎባ' (የስልጥኛ የጀግና ግጥሞች፤ ያልታተመ)።

8. ጎጎት (በጉራጌ ዞን ባህልና ስፖርት መምሪያ የተዘጋጀ)፥ 1987፥

ወልቂጤ።

9. ኤባ ጉት፤ ሁሴን መሐመድ፥ የስልጥኛ–አማርኛ–መዝገበ ቃላት፥ 1988።

10. ወርቁ ንዳ፥ ጀብዱ፥ አዲስ አበባ፥ 1983።

11. ዶክተር አብዱረህማን መሀመድ ቆራም፤ ማኽማኽ (የሐረሪ ተረትና

ምሳሌ)፥ መጋቢት 1984፥ አዲስ አበባ።

12. ሁሴንና አወል፥ 'የስልጤ ወጋ–ወግ' (የስልጤ ወግና ታሪክ፤ ያልታተመ)።

13. ዶክተር አብዱረህማን መሀመድ ቆራም፤ ጩቅቲ ክታብ (ሐረሪ–አማርኛ

መዝገበ ቃላት)፥ አዲስ አበባ፥ 1984።

14. የስልጤ ተውፊት

No comments:

Post a Comment